
የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ የአቶ ታደለ በቀለ መልዕክት
የየካ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በ2017 ዓ.ም ግማሽ በጀት ዓመት ጠንካራ የኮሙኒኬሽን ስርዓት በመዘርጋት፣ ዘመኑን የዋጀ የተሟላና ወቅቱን የጠበቀ መረጃና ማስረጃ ለክፍለ ከተማችን ነዋሪዎች በመስጠትና በመቀበል ተቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ዘርፍ የሚታዪ የተዛነፉ አመለካከትና እይታዎችን በመረጃና በማስረጃ በማስደገፍም ችግሮቹ እንዲቀረፉ በርካታ ዘገባዎችን በመስራት በመንግስትና በህዝቡ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል በግማሽ በጀት ዓመቱ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በተለይ በክፍለ ከተማና ወረዳ ደረጃ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ የቢሮ ማዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የሰራቸውን ተግባራት እንደ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በእቅድ በማካተትና ሁሉንም ተቋማት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ስራዎቻቸውን ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ በግማሽ በጀት ዓመቱ የመረጃ ጥራት፣ ሽፋንና ተደራሽነት አድማሳችንን ማስፋት ችለናል፡፡
የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ወቅቱ የሚጠይቀውን ጠንካራ የተግባቦት ስርዓት በመዘርጋት ፈጣን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለህዝባችን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ከማርካት ባሻገር ትክክለኛ መረጃን በማሰራጨት ህዝቡን ሊያሳስቱ የሚሞክሩ አካላትን አፍራሽ አጀንዳዎቻቸውን በየጊዜው ለይቶ በማውጣትና በማክሸፍ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ተግባር /አላማ/ በመጠቀም በመንግስት እና በህዝቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ጽህፈት ቤቱ በግማሽ በጀት ዓመቱ መረጃዎችን ተደራሽ ካደረገባቸውና እያደረገባቸው ካሉ መንገዶች አንዱ ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም ሲሆን በስድስት ወራት ከ7 በላይ የሶሻል ሚዲያ ፕላትፎርሞችን በመዘርጋት ለምሳሌ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም ወ.ዘ.ተ እና ዜናዎችን በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛና በአፋን ኦሮሞኛ ለማህበረሰባችን ተደራሽ ማድረጉን አጠናክሯል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደሩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና፣ በሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም በማዘጋጃ ቤታዊ የተሰሩ ተግባራትን የማሳወቅ፣ የማስገንዘብና የማስተማር ስራ በተለያዩ የኮሙኒኬሽን ተግባቦት ስራዎች በመስራት ተቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የህዝቡ እና የመንግስት አይንና ጆሮ በመሆን እየስራን ይገኛል ፡፡ በአስተዳደሩ የተሰሩ ስራዎችን በተለያዪ የኮሙኒኬሽን አግባቦች በአጭር ፕሮግራም፣ በዶክመንታሪ፣ በዜና፣ በህትመት ሚዲያው በብሮሸር፣ በበራሪ በመጽሄት፣ በተለያዪ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ስልቶችን በመጠቀም ከህዝብ ወደ መንግስት ከመንግስት ወደ ህዝብ መረጃን ለበጎ ነገር በመጠቀም ዘርፈ ብዙ ስራም ተሰርቷል፡፡
በክፍለ ከተማው ሁለንተናዊ ብልጽግና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ህብረተሰብ በመፍጠርና በአምክንዮ የሚያምን ሞጋች ትውልድ በማፍራት በተለያዩ የኮሙኒኬሽን አግባቦችን በመጠቀም ዘመናዊ፣ ግልጽ እና ፈጣን መረጃ በመስጠትና በመቀበል ባህሉ ያደረገ የኮሙኒኬሽን ስርዓት በመዘርጋትና በዘርፉ መሪ ተዋናይ በመሆን የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በመጨረሻም በክፍለ ከተማችን በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ያሉና የከተማዋን ከፍታ በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድጉ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን በተለያዪ የኮሙኒኬሽን አግባቦች በመስራት በዲጅታልና በህትመት ሚዲያ ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ መረጃ በመስጠት የተባበራችሁን አስፈጻሚ አካላት፣ የወረዳ ዘርፎቻችንና የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ላደረጋችሁት የነቃ ተሳትፎ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!!
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል !!
